
የዛሬ 27 አመት ገደማ የዩጎዝላቪያ ተወዳጅ ሙዚቀኞችና የስነ ጥበብ ባለሙያዎች በሚያዘጋጁት የሰላም ኮንሰርት የሚታደሙ ሁሉ በአንድ ነገር እርግጠኞች ነበሩ። በዩጎዝላቪያ ጦርነት ሊከሰት አይችልም፥ ሊኖርም አይገባም የሚል ከፍተኛ እምነት ነበራቸው።
ይሁንና፥ በጥቂት ፅንፈኛ ፓለቲከኞች የተመራው የጥላቻና የማስፈራራት ዘመቻው አሸናፊ ወደሌለው የለየለት ጦርነት ሃገሪቷን ማግዶ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ናዚ/ፋሽስት በአውሮፓ ካስከተለው እልቂት ወዲህ በአህጉሯ ታይቶ የማያውቅ እልቂት፥የሰዎች ጭካኔ፥የዘር ማጥፋትና ማፅዳት በሰፊው ተካሔደ፥ ዩጎዝላቪያም እንደ ሃገር መቆም ተሳናት በሗላም ፈረሰች።
በዚህ ባጠቃላይ ወደ 11 ዓመት በፈጀ ተከታታይና የተወሳሰበ ግጭት ወደ 2መቶ ሺህ በአብዛኛው ሰላማዊ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲሞቱ ተፈረደባቸው። ከ4 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎቿም እስከዛሬ ላልተቋጨ ስደት ተዳረጉ። ሌላም ሌላም ብዙ መከራ ደረሰ።